በሀረሪ ክልል በተቋማት የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ አንፃር መሻሻል መታየቱ ተገለፀ
ሐረር፤የካቲት 5/2017(ሀክመኮ):- በሀረሪ ክልል በሚገኙ የመንግስት ተቋማት የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ አንፃር መሻሻሎች መኖራቸውን የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ኃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዚነት ዩሱፍ እንደተናገሩት ባለፉት 6 ወራት በመንግስት ተቋማት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል።
የመልካም አስተዳደር ምንጭ የሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመቅረፍ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የአገልግሎት አሰጣጥ ሰርዓቱን በማሻሻል ከወረዳ ጀምሮ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ አንድ በማምጣት ወጥ እንዲሆኑ ለማስቻል የዜጎች ቻርተር ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱንም ገልፀዋል።
ይህም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው ሲነሱ የቆዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ በማሳደግ ረገድ መሻሻሎች እንደታዩ ነው የገለፁት።
በቀጣይም የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ በእውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት የዳበረ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እንደሚሰራ ወይዘሮ ዚነት ዩሱፍ አክለዋል።
0 Comments