Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በሀረሪ ክልል ለመንገድ ደህንነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው- ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር

ሀረር ሰኔ 19/2016(ሀክመኮ):-በሀረሪ ክልል ለመንገድ ደህንነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ገለፁ።

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ድኤታ የተመራ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዑካን ቡድን ከሀረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ዙሪያ መክሯል።

በምክክሩ ላይም የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር  በክልሉ ለመንገድ ደህንነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ክልሉ ሁለት ቅርሶችን በአለም አቀፍ ቅርስነት በዩኔስኮ ያስመዘገበ እንዲሁም ሜዲካልን ጨምሮ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የያዘ መሆኑን በመጠቆም ዘርፉን ይበልጥ ለማጎልበት የሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ካሉ 3 የካንሰር ህክምና ማዕከላት አንዱ በሀረር የሚገኝ በመሆኑ እንደ ሶማሊያ ካሉ ጎረቤት አገራት ብሎም ከአጎራባች ክልሎች በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች በየ ዕለቱ የሚስተናገዱበት ክልል መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሉ በጅቡቲ ወደብ አቅራቢያ እንደመገኘቱ ሀረርን ከድሬደዋ እና ጅጅጋ የሚያገናኙ መንገዶች እንግልት የሚቀንሱ እና ለትራንስፖርት የተመቹ ሊደረጉ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በክልሉ በተለይ ህገ ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ እና ግንባታዎችን ስርዓት በማስያዝ ምቹ የብስክሌት እና እግረኛ መንገዶችን የያዘ የኮሪደር ልማት እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከብቃት ማነስ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል የመንጃ ፍቃድ አሰጣጡን ዲጂታል በማድረግ  ከሙስና የማጥራት ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በቀጣዩ 2017 የስራ ዘመን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ዘርፉን ይበልጥ ለማጠናከር ዕቅድ መያዙንም አክለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የትራንስፖርት እና ቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አቶ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፍሬ እንዲያፈራ ለማስቻል የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚና የማይተካ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የግብርና ምርቶች ሳይበላሹ ለገበያ ቀርበው ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል ለምርቱ የተመቹ ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል አምራች የሆነውን የሰው ሀይል እና ኢኮኖሚ እያወደመ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ለመንገድ ደህንነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሰገንዝበዋል ።

እንደሀገር የጋማ ከብቶችን በመጠቀም  እስታንዳርዱን የጠበቀ መጓጓዣ ብሎም ነዳጅ አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ እንዲውል ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን እውን ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት የሚጠይቁ በመሆኑ አመራሩ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ሚኒስትር ድኤታው መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish