ሴቶች በሀገሪቱ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ- ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም
ሐረር፤የካቲት/29/2017(ሐክመኮ):-ሴቶች በሀገሪቱ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ የሐረሪ ብሄራዊ ጉባኤ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም ገለፁ።
አለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8)”ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪቃል በሐረር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
የሐረሪ ብሄራዊ ጉባኤ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶች በሀገሪቱ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።
የክልሉ መንግስት የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የአመራርነት ሚናቸውን ለማሳደግ ትኩረት ሰቶ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ምክትል አፈ ጉባኤዋ አክለው ገልፀዋል።
ዕለቱን በማስመልከት የተዘጋጀው ባዛርም የአምራች ሴቶች ምርትን በማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስር በመፍጠር አበርክቶው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የገለፁት ደግሞ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ ናቸው።
ዕለቱ ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን መድሎና መገለል ለማስቀረት የተደረገው ትግል የሚዘከርበት እና የስርዓተ ጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ ሴቶች ከነበረባቸው ተጽዕኖ ተላቀው በኢኮኖሚያዊ፣በማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት የተመዘገቡ ለውጦችን ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የሐረሪ ክልል የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ረምዚያ አብዱልወሃብ በበኩላቸው ቀኑ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገባቸውን ስፍራ እንዲያገኙ ትልቅ መሠረት የጣለ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ ሴቶች የብድርና ቁጠባ አገልግሎት መመቻቸቱን ብሎም ምርት እና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ፤ የገበያ ትስስር በመፍጠር የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የንግድ ባዛሮች መዘጋጀታቸውንም አክለዋል።
ዕለቱን በማስመልከት የተዘጋጀ ባዛር የተከፈተ ሲሆን በስነ-ስርዓቱ ላይ የሐረሪ ብሄራዊ ጉባኤ ምክትል አፈ ጉባኤን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።



0 Comments