ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በማስፋት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በማስፋት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህጻናትን በቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቀብለናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጤናን እና ትምህርትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በማስፋት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በጤናው ዘርፍ ከ22ሺህ ገደማ ተቋማት መካከል 6ሺህ ያህሉ ከለውጡ ወዲህ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው የግል ዘርፍ የህክምና ተቋማትም እየተስፋፉ ነው ብለዋል።
ሆኖም አሁንም ችግር አለ፣ ከመሰረተ ልማትና ከጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አንጻር ምላሽ እየሰጠን መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።
ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በማስፋት የጤና ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ነው ጨምረው የተናገሩት።
በትምህርት ዘርፍም በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህጻናትን በቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቀብለናል ብለዋል።
26ሺህ ደግሞ የልዩ ፍላጎት ህጻናት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ልክ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባትና መምህራንን ማፍራት ላይም ሰርተናል ነው ያሉት።
የመምህራን ልማትን በሚመለከት ወደ 68ሺህ መምህራን ሰልጥነዋል፤ ዘንድሮ 80ሺህ መምህራን በትምህርትና መማር ማስተማር ይሰለጥናሉ ሲሉም ገልጸዋል።
30 ገደማ ሞደል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመው ማህብረሰቡ በትምህርት ለትውልድ ባዋጣው ገንዘብ፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመፅሐፍና ትምህርት ጥምርታን ማሟላት ተችሏል ብለዋል።
እነዘህን ተግባራት እያጠናከርን ስንሄድ ተጨባጭ ውጤት ይመጣል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ።
0 Comments