Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

መገናኛ ብዙኃን ህግና መመሪያን መሰረት በማድረግ ሕዝብን የሚጠቅሙና ሀገርን የሚያሻግሩ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ።

የኢትዮጵያ መገናኛ  ብዙኀን ባለሥልጣን የላይዘን ቢሮውን በሐረር ከተማ በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የቢሮው ኦፊሰር አቶ መሐመድ ሱሌ እንደገለፁት ባለሥልጣኑ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እና የነበረበትን የተደራሽ እጥረት ለማቃለል በማሰብ ቢሮውን በሐረር ከተማ መክፈቱን ተናግረዋል። 

ባለሥልጣኑ ቢሮው ሐረሪ ክልል መከፈቱ አገልግሎቱን የሚሹ በክልሉ እና አከባቢ የሚገኙ ተገልጋዮች ወደ አዲስ አበባ ከመሄድ እንዳስቀረላቸው ጠቁመው ይህም የተገልጋዩን የጊዜ፣ የገንዘብ እና የጉልበት ወጪ እንዳስቀረ ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/ 2013 መሠረት በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኀን እና የማስታዎቂያ አገልግሎት ዘርፎችን የመቆጣጠር እና የመደገፍ ኃላፊነት እንደተሰጠውም ኦፊሰሩ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ባለስልጣኑ የተለያዩ ሙያዊና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

የሕዝብ፣ የንግድ፣ የማኅበረሰብ፣ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እና  የማስታዎቂያ ዘርፎች ሕጋዊ ሆነው እና ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረው እንዲሰሩ የሚያግዝ ሥልጠና ይሰጣል፣ ይቆጣጠራል፣ ድጋፍም ያደርጋል ብለዋል፡፡ 

ባለሥልጣኑ በክልል ደረጃ ቢሮ ከፍቶ እየሠራ ስለመሆኑ አብዛኛው ተገልጋይ ግንዛቤ የለውም ያሉት አቶ መሐመድ አገልግሎቱን የሚሹ የሚዲያ ተቋማት እና የማስታዎቂያ ዘርፎች ተገቢውን አገልግሎት ከላይዘን ቢሮው ማግኘት እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም በግልም ይሁን በቡድን ሚዲያ ማቋቋም የሚፈልጉ ሁሉ የሙያ ፈቃድ፣ እድሳት እና  ሌሎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ነው ያብራሩት፡፡

በሐረሪ ክልልና አከባቢ የሚገኙ የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ሕግን መሠረት አድርገው እየሠሩ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ይህንን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ሕጋዊ የሚዲያ ተቋማት ሕዝብን እና ሀገርን የመጥቀም አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሐሰተኛ መረጃን፣ የጥላቻ ንግግርን በሚያሰራጩ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለመሥራት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ህዝቡ ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ አካላት በቢሮው የነጻ ስልክ መስመር 9192 ላይ በመጠቆም ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡ 

ሚዲያዎችም ሙያዊ ስነምግባር በተላበሰ መልኩ ሰላምን፣ አብሮነትን እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ለህዝቡ ተደራሽ የማድረግ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish