Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

መንግሥት የነዳጅ ድጎማ የሚያደርገው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ጫና ለማቅለል እንጂ ጥቂት ግለሰቦችን ለመጥቀም አይደለም

መንግሥት የነዳጅ ድጎማ የሚያደርገው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ጫና ለማቅለል እንጂ ጥቂት ግለሰቦችን ለመጥቀም አይደለም ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባቷን ጠቅሰው፤ ይህም የተረጋጋ ኢኮኖሚ በመፍጠር የንግድና ኢንቨስትመንት አካባቢዎችን ማሻሻል የዘርፎችን ምርታማነት ማሻሻልና የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ማጎልበትን ያተኮረ ነው ብለዋል።

በዚህም የግል ዘርፉን ተሳትፎ ያገናዘበ ብዝሃ ዘርፍን መሰረት ያደረገና ሚዛናዊ ትኩረትን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ መወሰኑ አምራቾች ከሚያመርቱት በቂ ትርፍ እንዲያገኙ፣ የኮንትሮባንድና ህገወጥነትን የሚቀርፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ማሻሻያው ህገ ወጥነትን ወደ ህጋዊ አሰራሮች እንዲገቡ በማድረግ የተራራቁ ገበያዎችን የማቀራረብ ስርዓትን ፈጥሯል ነው ያሉት።

የምንዛሬ ተመኑ በገበያ መወሰኑ ወደ ማዕከላዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ አቅርቦት በእጅጉ እንዲጨምር ማስቻሉን ገልጸዋል።

በቡና፣ በቅባት እህሎች፣ በጥራጥሬ፣ በኢንዱስትሪ ምርቶችና በአገልግሎት የሚገኘው የምንዛሬ መጠን እንዲጨምር ማድረጉንም ተናግረዋል።

አርሶና አርብቶ አደሮች የልፋት ዋጋቸውን እንዲያገኙ፣ ተኪ ምርት ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ አመራቾች ተጠቃሚነትም እያጎለበተ ነው ብለዋል።

ማሻሻያው መንግስት ከልማት አጋሮች በሚያገኘው ድጋፍና ብድር አንገብጋቢ የልማት ስራዎችን ለማከናወን በቂ ሀብት እንዲያገኝ ማስቻሉን ጠቁመው፤ ለገበያ መረጋጋትና ለስራ ዕድል ፈጠራ መዋሉን ገልጸዋል።

የብሔራዊ ባንክ ያጸደቀው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ መንግሥት ከግምጃ ቤት የሚበደረው ቦንድ እንዲገደብ እንዲሁም ባንኮች የብድር መጠን በ18 በመቶ እንዲገደብ በማድረጉ በገበያ ውስጥ መረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።

ይህም የዋጋ ንረቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ገልጸው፤ የባንኮች የቁጠባ መጠን እንዲጨምር ማድርጉንም ጠቁመዋል። 

ሊመጡ የሚችሉ የዋጋ ጭማሪዎች በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የተደረጉ ሪፎርሞች ያለምንም እንቅፋት እንዲተገበሩ መንግስት ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በዚህም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች እንዳይጎዱ ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ መደረጉን ገልጸዋል።

የድጎማው ተጠቃሚዎች በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ መሆናቸውን እያረጋገጡ መሄድ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ለነዳጅ ከሚደረገው ድጎማ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በየጫካው በርካታ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ተደብቀው መገኘታቸውን ጠቁመው፤ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።።

መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያ የሚያደርገው ድጎማ ምርታማነትን በመጨመር ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ መሆኑንም ገልጸዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish