ሐረርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሐረርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ የፕሮጀክት ግንባታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለፀ።
በከተማው የሚገነቡ የመሰረተ ልማትና የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ እያሻገረና የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ዮኒስ ለኢዜአ እንደገለጹት ሐረርን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ ስራ በከተማው በተለያዩ ስፍራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በተለይ በከተማው በአዲስ እየተገነቡ እና እየታደሱ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
በከተማው የኮሪደር ልማትም እስከ 30 ሜትር ስፋት ያለው የአስፓልት መንገድ ግንባታም እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው የግንባታ ስራዎቹ እየተፋጠኑ መሆኑን አመልክተዋል።
ከጽዳት ጋር በተያያዘም በቀን ሶስት ጊዜ የደረቅ ቆሻሻን በማንሳት ከተማዋን ጽዱ የማድረግ ሰራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዋሪውና ጎብኚው ወጣ ብሎ የሚናፈስበት፣ አየር የሚወስድበትና ሻይ ቡና እያለ መጽሃፍ የሚያነብበት ስፍራ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ለዚህም በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በከተማው በህገ ወጥ ንግድና በሌሎች ተግባራት የተያዙና ህብረተሰቡን ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርጉ የነበሩ የእግረኛ መንገዶች ባለፉት ሶስት ወራት የማስከፈትና የማልማት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የሚያከናውነው የልማት ስራ ነዋሪውንና ጎብኚውን የሚያረካና ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ እየለወጠ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል።




0 Comments