Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የፀጥታ ተቋማት እና ደንብ አስከባሪዎች ደንቡን በማስፈፀም ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል-የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት

የፀጥታ ተቋማት እና ደንብ አስከባሪዎች ተሻሽሎ የፀደቀውን የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ደንብ በማስፈፀም ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈርሀን ዚያድ ገለፁ።

የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ማቋቋሚያ እና ተሻሽሎ ወደ ስራ የገባው የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ደንብ ላይ በክልሉ ለሚገኙ የፀጥታ ተቋማት እና ደንብ እስከባሪዎች ግንዛቤ ፈጥሯል።

የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈርሀን ዚያድ በክልሉ ሲስተዋል የነበረው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ የከተማውን ገፅታ ማበላሸቱን አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት ለከተማው ፅዳት እና ውበት በሰጠው ትኩረት ከተማዋን ፅዱ እና ውብ ማድረግ  ማስቻሉን ገልፀው የከተማውን ፅዳት በዘላቂነት ለማስበቅ ቀድሞ የነበረውን የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ደንብ አሻሽሎ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።

አዲስ ተሻሽሎ የፀደቀው ደንብ በከተማው የሚገኙ ድርጅቶች እና ማህበረሰብ በከተማው ፅዳት የበኩላቸውን አሻራ እንዲያኖሩ በማስቻል  ቀድሞ የነበረውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር በመቅረፍ ፅዱ እና ውብ ከተማን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ደንቡ ክልከላዎችን ጨምሮ አስገዳጅ ህጎችን በውስጡ የያዘ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ስራ አስኪያጁ የፀጥታ ተቋማት፤ የመንገድ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች እና የደንብ አስከባሪዎች ለደንቡ ተፈፃሚነት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሀረሪ ክልል ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ ምክትል ኮሚሽነር ነስሪ ዘከሪያ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ተቋማት ለደንቡ ተፈፃሚነት አስፈላጊውን የክትትል እና ቁጥጥር ስራ እንዲያከናውኑ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይም በደንቡ ላይ የተቀመጡ መቀጮዎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ በማመላከት ማህበረሰቡ ለደንቡ ተገዢ በመሆን የከተማውን ፅዳት በሀላፊነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ የሀረሪ ክልል  ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገናነው ጥበቡን ጨምሮ የክልሉ የፀጥታ ተቋማት ፤የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት፤የትራፊክ እና የመንገድ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች ተሳትፈዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

aoAfaan Oromo