የደስታ መግለጫ
- የተከበራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች
- የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች
- በዓለም ዙሪያ የምትገኙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች፣
~~~
ዛሬ በዚህ ታሪካዊ ቀን፣ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በብዙ ውጣ ውረዶች ያለፈው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በላቀ ድምቀት ለምረቃ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ ለማለት እወዳለሁ።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በትውልዶች ሕልም ላይ የብሔራዊ መግባባት፣ የአንድነትና የሉዓላዊነት ሀውልት መቆሙን የሚያበስር ነው።
ይህ ከአፍሪካ አንደኛ እና በዓለም ከተገነቡ ግዙፍ ግድቦች መካከል አንዱ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለዘመናት መገለጫችን የነበረውን የድህነት ክበብ በመስበር በዘርፉ የነበረንን የታሪክ ጉድለት ከመሰረቱ የሚለውጥ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ድል ነው።
በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ እውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ መገንባቱም የነጻነት፣ የኩራት እና የስኬት ተምሳሌት ያደርገዋል።
በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እና ወንድም ህዝቦችም ‘በይቻላል!’ ስሜት የሚፈጥረው መነሳሳትም አባቶቻችን ለነጻነት ያደረጉት ትግልና የተቀዳጁት ድል ካቀጣጠለው አፍሪካዊ የነጻነት ንቅናቄ የማይተናነስ ነው።
ይህ ግድብ የድህነትን ጨለማ የሚያስወግድ እና የብልጽግና ብርሃንን የሚያደምቅ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያን ጥንካሬ እና ጽናት ማረጋገጫ ማህተም ነው፤ በራስ መተማመንን የሚያጎላ ምልክት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ክንድ እና የመሪነት አቅም ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ እጣ ፈንታዋን በገዛ እጆቿ እና ልጆቿ የመወሰን አቅም እንዳላት ምስክር ነው።
የሕዳሴው ግድብ ለቀጣይ ትውልዶች የቆመ ትልቅ ቅርስ ነው። ለብዙ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጥም ነው። የኢንዱስትሪ ልማትን የሚያፋጥን እና የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኛም ነው። ይህ ግድብ፣ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለቀጠናው የልማት እና የሰላም ማዕከል የሚሆን ነው።
የዛሬው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ አዲስ ዘመን ብስራት እና ስጦታ ብቻ ሳይሆን ‘ሁለተኛው አድዋ’ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው የክፍለ ዘመኑ የኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል አንጸባራቂ ድል ነው፤ በአዲስ ዓመት የአዲስ ምእራፍ እና የመንሰራራት ዘመን ትንሳኤ ነው።
በመጨረሻም የህዳሴ ግድብን የመሰለ ታላቅ ፕሮጀክት ማስጀመር ግብ አይደለም፤ በአንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር ይቻላል። ጅምሮች ትርጉም የሚኖራቸው ግን በታለመለት ጥራት እና ጊዜ ተገንብተው ሲጠናቀቁ፣ ሲመረቁና አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ነው።
በዚህ ረገድ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በጅምር እንዳይቀር፣ ሥራው እንዲፋጠን፣ በጥራት እንዲሰራ፣ እንዲጠናቀቅና ለዛሬው ምረቃ እንዲበቃ ጠቅላይ ሚንስትር ዶር አቢይ አህመድ ላበረከቱት የላቀ የመሪነት ሚና፣ ለሰጡት ያልተቋረጠ አመራርና ሁለንተናዊ ድጋፍ በራሴ፣ በሀረሪ ክልል ህዝብና መንግስት ስም ልባዊ አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ። በዚህ ታላቅ የመሪነት ሚናቸው የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን መጪው የኢትዮጵያ ትውልድ እና ታሪክም ከአድዋ ድል ታላላቅ መሪዎች እኩል እንደሚያስታውሳቸውና ወርቃማ ሀውልት እንደሚያቆምላቸው እምነቴ የጸና ነው።
የዚህ ዘመን፣ የዚህ ታሪካዊ ክስተት፣ የዚህ ትውልድና የአመራር አካል እንዲሁም የዚህ የላቀ ሁነት እና የደስታ ስሜት ተካፋይ በመሆናችን በድጋሚ እንኳን ደስ አለን፤ ደስ አላችሁ፤ እንኳን በአዲስ ዘመን ታላቅ ብስራት ለአዲስ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁ – አደረሰን።
ኦርዲን በድሪ
የሀረሪ ህዝብ ክልል ፕሬዝዳንት
ጳጉሜ 4/2017 – ጉባ
0 Comments