Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የሀረሪ ክልል የፀጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ተወያይቷል።

በሀረሪ ክልል እየተስተዋለ የሚገኘው አንፃራዊ ሰላም ወደ አወንታዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ይገኛል።

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት በክልሉ ሰላም እንዲጠናከር በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል።

የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እንዳይሰፍን የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታ ምክር ቤቱ በቁርጠኝነት ይሰራል።

መጪው የዳመራና የመስቀል በዓላትም ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቁም በተለይ የፀጥታ ሀይልን በማጠናከር፣ በተመረጡ አካባቢዎች ተገቢውን ፍተሻና ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ህዝብን በላቀ ደረጃ በማቀናጀት በትኩረት ይሰራል።

ከዚህ በተጨማሪ የማህበራዊ ሚዲያን ለእኩይ ዓላማ በማዋል ህዝብን ከመንግሥት፣ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩ መልዕክቶችን በመቅረጽ በማህበራዊ ሚዲያ ሀሰት መረጃ በሚያሰራጩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ምክር ቤቱ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል።

በክልሉ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች እና በመልካም አስተዳደር ችግር ህዝብን የሚያማርሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ምክር ቤቱ በመግለጫው አመላክቷል።

የክልሉን ሰላምና ጸጥታን የማስፈን እና ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ዛሬም እንደ ትላንቱ የክልላችን ህዝቦች ለሰላም ዘብ እንዲቆም ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።

የሀረሪ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት
መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም
ሀረር

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

aoAfaan Oromo