በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በዛሬው ዕለት ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው 6ተኛ ዙር 4ተኛ ዓመት 8ተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማጎልበት የተከናወኑ ተግባራትን ርዕሰ መስተዳድሩ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ በማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከ 33 ሺ በላይ አባወራና እማወራዎች ተጠቃሚ ተደርገዋል።
ከዚህው ውስጥም ከፍለው መገልገል ለማይችሉ 7 ሺ 478 አቅመ ደካማ ዜጎች ወጪ በክልሉ መንግስት እንዲሸፈን መደረጉን አክለዋል።
በበጀት ዓመቱ ባጠቃላይ ከ 26 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማውጣት ለ 146 ሺ 530 አባላት በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳለጥ የመድሀኒት አቅርቦትን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራትም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
እናቶች ጥራት ያለው የወሊድ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎት አንዲያገኙ በማስቻል የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግቧል።
በተለይ የአተነፋፈስ ችግር ገጥሟቸው የሚወለዱ ህፃናትና ጨቅላ ህፃናትን አክሞ በማዳን አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን በመጠቆም በቀጣይ የህፃናት ሞትን ይበልጥ ለመቀነስ በትኩረት ይሰራል።
ሁሉንም አይነት ክትባቶች ያገኙ ህፃናትን ሽፋን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ዕቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን በቀጣይ አገልግሎቱን በማጎልበት ክትባት የሚያቋርጡ ህፃናት ክትባቱን እንዲያገኙ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል።
ኤች አይቪ ከእናት ወደ ፅንስ እንዳይተላለፍ ለማስቻል በተከናወነው ተግባር የነብሰ ጡርና አጥቢ እናቶች የፀረ ኤች አይቪ አገልግሎት ሽፋንን ከነበረበት 88 በመቶ ወደ 96 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
በተለይ በወባ በሽታ የሚሞቱ ህሙማንን ለመቀነስ በተከናወነው ተግባር 0 ሞት በማስመዝገብ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
በጁገል ሆስፒታል በተጀመረው የኩላሊት ትጥበት 1 ሺ 176 ታካሚዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በጤና ተቋማት ለዜጎች ጥራት ያለው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በተሰራው ስራ የስነ ምግባር ጉድለት የተስተዋለባቸው ባለሞያዎች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዷል።
በተለይ በግል ጤና ተቋማት ከህብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ፋርማሲዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
0 Comments