በከተማው የወንዝ ዳርቻ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
በሀረር ከተማ የወንዝ ዳርቻ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በሀረር ከተማ በሚገኙ ወንዞች ላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱ 800 ሜትር ርዝመትና 80 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በ 6 ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን መሆኑ በከተማ ማዘጋጃ ቤቱ በቀረበው ዲዛይን ተመላክቷል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንደገለፁት በከተማው የሚገኙ ወንዞችን ከብክለት የፀዱ፣ውብና ማራኪ ለማድረግ ይሰራል።
የወንዝ ዳርቻ ልማት ለነዋሪው ጤናማ ህይወት እና ለአካባቢ ዘላቂ ልማት ወሳኝ አስተዋፅኦ ከማበርከቱም በላይ የከተማዋን ገፅታ የመቀየር አቅም እንዳለው ገልፀዋል።
በተለይ ከተማዋ ንጹህ ወንዞች የሚፈሱባት፣ፅዱና ውብ እንድትሆን በማስቻል ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።
ይህን እውን ለማድረግም ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሾችን በስርዓቱ ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በቀጣይ በአጭር ግዜ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ እንዲገባም ርዕሰ መስተዳድር አቶ አርዲን በድሪ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።



0 Comments