Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድል ለሌሎች ስኬቶች መነሳሳትን የፈጠረ ነው- አቶ ጌቱ ወዬሳ

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድል መነሳሳትን የፈጠረና ለሌሎች ፕሮጀክቶች ከፍ ያለ እሳቤን ያጎናጸፈ መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።

በሀረሪ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የማስ ስፖርት ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች የስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ህልማቸውን በጋራ ያሳኩበት ፕሮጀክት ነው።

የክልሉ ነዋሪም ለስኬቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመንቀሳቀስ ግድቡ እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋዕኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የላብ፣ የደም እና የእንባ ውጤት መሆኑን ነው አቶ ጌቱ የገለጹት።

በሕዳሴ ግድብ የተመዘገበው ድልም ለሌሎች ስኬቶች መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከፍ ያለ እሳቤን የፈጠረ ነው ብለዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን እንደሚችሉ ለዓለም ያሳዩበትና ህልማቸውን በጋራ ያሳኩበት ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቅሰው፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከሀብታም እስከ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በመረባረብ በጋራ ያሳኩት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁንም በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በህብረት ይበልጥ መረባረብ አለብን ብለዋል።

በመርሀግብሩ ላይ ያገኘናቸው ተሳታፊዎች እንዳሉት በሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የህብረት ተምሳሌት እና የጽናት ምልክት ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ አንድነታችንን በማጠናከር በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችም በጋራ መቆም ይኖርብናል ብለዋል።

በመርሃግብሩ ላይ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሮዛ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

aoAfaan Oromo