ማህበረሰቡ ለደንቡ ተገዢ በመሆን የበኩሉን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባል የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት::
ማህበረሰቡ ተሻሽሎ ለፀደቀው ደንብ ተገዢ በመሆን ለከተማው ውበት እና ገፅታ የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣ የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈርሀን ዚያድ ጥሪ አቀረቡ።
የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ማቋቋሚያ እና የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደርን ለማሻሻል እና የአሰራር ስርዓትን ለመወሰን ተሻሽሎ በፀደቀው ደንብ ላይ ለክልሉ ማህበረሰብ ግንዛቤ ፈጥሯል።
የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፈርሀን ዚያድ ከተማውን ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች የተመቸች ለማድረግ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መመዝገባቸውን በግንዛቤ ማስጨበጫው ላይ ገልፀዋል።
በተለይ በክልሉ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ምቹ የእግረኛ እና የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ከማስቻል ባሻገር ከተማዋን ውብ ገፅታ ያላበሰ መሆኑን አመላክተዋል።
በክልሉ ተግባራዊ የሆኑ የመሰረተ ልማቶችን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ የገለፁት ምክትል ስራ አስኪያጁ ተሻሽሎ የፀደቀው ደንብ የኮሪደር ልማቶችን ከጉዳት ለመከላከል ብሎም የከተማውን ውበት እና ጽዳት ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አክለውም የአካባቢ ብክለትን በማስቀረት የከተማውን ማህበረሰብ ጤናና ደህንነት ለማረጋገጥ እና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ስርዓት በከተማዋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መስተጓጎል እንዳይፈጠር ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ደንቡ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታን በማስቀረት በክልሉ ያለውን ውስን የመሬት ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።
በተለይ አዲስ በተሻሻለው ደንብ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታ ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ባሻገር የብር መቀጮ የሚያስከትል መሆኑን በመገንዘብ ማህበረሰቡ ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ደንቡ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ የዋለ በመሆኑ ማህበረሰቡ በደንቡ ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን በመከልከል እራሱን ከቅጣት ሊጠብቅ እንደሚገባ ምክትል ስራ አስኪያጁ መልዕክት አስተላልፈዋል።



0 Comments